የሀገር ውስጥ ዜና

አርቲስት አብነት ዳግም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

By Melaku Gedif

August 09, 2023

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አርቲስት አብነት ዳግም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ለረዥም ጊዜ በህመም ላይ የቆየው አርቲስት አብነት በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

አርቲስት አብነት በበርካታ ቴአትሮች ፣ ፊልሞች እና ድራማዎች ላይ በተዋናይነት በመሳተፍ እውቅናን ያተረፈ ነበር።

ከዚህ ውስጥ አሉላ አባነጋ፣ የቼዝ ዓለም፣ ዳኛው፣ እስረኛው ንጉስ እና ነቅዕ ቴአትሮች ላይ ተውኗል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አያስቅም፣ አንድ እድል፣ ላምባዲና፣ ሰበበኛ፣ ባንቺ የመጣ፣ ቁልፉን ስጭኝ፣ የነገርኩሽ እለት፣ ፍቅር እስከ መቃብር እና አትሸኟትም ወይ በተሰኙ ፊልሞች ላይ በመተወን አድናቆትን አግኝቷል።

ስንቅ ፣መለከት፣ ትርታ እና ለወደዱት ደግሞ የተሳተፈባቸው ቲቪ ድራማዎች ሲሆኑ፥ በግሉም የቅብብሎሽ ድራማን ደርሷል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በአንጋፋው አርቲስት አብነት ዳግም ህልፈት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል፡፡