ዓለምአቀፋዊ ዜና

በጀልባ መስጠም አደጋ የ41 ፍልሰተኞች ህይወት አለፈ

By Tamrat Bishaw

August 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣልያን ላምፔዱሳ ደሴት በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ የ41 ፍልሰተኞች ህይወት ማለፉን ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ተናግረዋል።

ከአደጋው የተረፉ አራት ሰዎች ለነፍስ አድን ሰራተኞች እንደተናገሩት፤ አደጋው የደረሰው ፍልሰተኞችን አሳፍራ ከቱኒዚያ ስፋክስ ተነስታ ወደ ጣሊያን በምትጓዝ ጀልባ ላይ ነው።

ከኮትዲቭዋር እና ከጊኒ የመጡት በህይወት የተረፉ አራቱ ግለሰቦች በዛሬው ዕለት ላምፔዱሳ መድረሳቸው ተነግሯል።

በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከ1 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ ህይወታቸውን አጥተዋል።

በአውሮፓ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ለሚጓዙ ፍልሰተኞች ታዋቂ መግቢያ ተደርጋ የምትቆጠረው የቱኒዚያዋ የወደብ ከተማ ስፋክስ ከጣሊያኗ ላምፔዱሳ ደሴት በ130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

ወደ ደሴቲቷ በሚደረግ የፍልሰተኞች ህገ-ወጥ የባህር ላይ ጉዞ ተደጋጋሚ አደጋ እያጋጠመ ህይወት ይጠፋል።

በቅርብ ቀናት ውስጥ የጣሊያን የጥበቃ ጀልባዎች እና የበጎ አድራጎት ቡድኖች ላምፔዱሳ የደረሱ ሌሎች 2 ሺህ ሰዎችን መታደግ መቻላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።