የሀገር ውስጥ ዜና

ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሠራ ተመለከተ

By Tamrat Bishaw

August 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሠራ ገለጹ፡፡

በሴንት ፒተርስበርግ የተደረገውን የሩሲያና አፍሪካ ጉባዔ በተመለከተ አምባሳደሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም÷ ሩሲያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በተለያየ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ያላትን ፍላጎት ያሳየችበትና ግንኙነቷን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች የተደረጉበት መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያና ሩሲያ ከጉባዔው ጎን ለጎን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች መፈራረማቸውን ገልጸዋል።

ስምምነቶቹ በመተማመን ላይ የተመሰረተውን የኢትዮ-ሩሲያ ታሪካዊ ግንኙነትና ትስስር ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያግዙ ጠቁመዋል።

በንግድ እንቅስቃሴ የሚያጋጥሙ ከቀረጥ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን በጋራ በመቅረፍ የተጀመረውን የንግድ ትስስር ለማሳለጥ ሩስያ ቁርጠኛ ስለመሆኗም አንስተዋል፡፡

ሩሲያ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የምትሰጠውን ነጻ የትምህርት ዕድል አሳድጋለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሀገራቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ጠንካራ የትምህርት ትብብር እንዲመሰረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ የሩሲያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት ዕድል ይመቻቻል ብለዋል፡፡

በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍም በሁለቱ ሀገራት መካከል ትብብር መጀመሩን አስገንዝበዋል፡፡