የሀገር ውስጥ ዜና

በምርመራ ኦዲት 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ተገኘ

By ዮሐንስ ደርበው

August 10, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሕገ-ወጥ ግብይትና ታክስ ማጭበርበር ድርጊት ጋር ተያይዞ በተከናወነ የምርመራ ኦዲት ድርጅቶች ለመንግሥት ያልከፈሉት 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መገኘቱን ገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ድርጅቶቹም ግኝቱን ጨምሮ ከወለድና ቅጣት ጋር 12 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር እንዲከፍሉ መወሰኑን በሚኒስቴሩ የታክስ ማጭበርበር ምርመራ የሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሲሳይ ገዙ ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 528 ድርጅቶች ላይ የምርመራ ኦዲት መከናወኑንም ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡

ኦዲት ከተደረጉ ድርጅቶች መካከል 322 ድርጅቶች ሐሰተኛ ደረሰኝ ወይም ሀሰተኛ ግብይት ተጠቅመው የታክስ ማጭበርበር ተግባር መፈጸማቸው መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም ትክክለኛ ገቢን አለማሳወቅና ከተቀበሉት ዋጋ በታች ደረሰኝ መቁረጥ የሚሉ ወንጀሎችን ፈጽመዋል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል የሐሰተኛ ደረሰኝ ሥርጭትን ከምንጩ ለመከላከል በተሰራ ስራ ሐሰተኛ ደረሰኝን በማተም እና ማሰራጨት ወንጀል ተሳትፈዋል የተባሉ 2 ማተሚያ ቤቶችን ጨምሮ 10 ሕገ ወጥ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል፡፡

ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ 14 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

በግብይት እና በአገልግሎት ጊዜ ደረሰኝ አለመስጠት ሌላው ወንጀል መሆኑን ገልጸው÷ ደረሰኝ ሳይቆርጡ የተገኙ 568 ድርጅቶች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋልም ነው ያሉት፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም 834 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን እና ክስ የተመሠረተባቸው ስለመኖራቸውም አንስተዋል፡፡

በታክስ ማጭበርበር ድርጊት መሻሻል የታየባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም የማጭበርበር ድርጊቶች መልካቸውን ቀይረው እየመጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም በሕጋዊ ግብር ከፋዮች ስም አስመስሎ ደረሰኝ የማዘጋጀትና የማሰራጨት ድርጊት እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡

የታክስ ስወራ አሁንም በሚፈለገው ልክ አለመቀነሱን አንስተው÷ ከሕግ ማስከበሩ ጎን ለጎን የግንዛቤ ፈጠራው ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!