አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 29፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከኮሮናቫይረስ ወረረሽኝ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ 4 ነጥብ 7 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል አለ።
ድርጅቱ ተጨማሪ ድጋፉ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና የጤና ስርዓታቸው ደካማ በሆኑ አገራት ውስጥ የሚኖሩ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ የሚውል ነውም ብሏል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ዋና ፀሀፊ ማርክ ሎውኮክ፥ በዓለም ላይ በጣም ደሃ በሆኑት አገሮች ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያስከትለው ጉዳት ከባድ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም አሁን እርምጃ ካልወሰድን በስተቀር ወረርሽኙ ግጭት፣ ረሃብ እና ድህነትን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
አክለውም ለጋሽ ሀገሮች የራሳቸውን ቀውስ ከማስተናገድ ባለፈ ድሃ አገሮችን ለመርዳት ከ900 ሚሊየን ዶላር በላይ ቃል መግባታቸውን አስታውሰው ነገር ግን ችግሩን ለመቋቋም ከዚያ በላይ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
ከዚያም ባለፈ ለወረርሽኙ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ 50 ሀገራት ዝርዝር በተጨማሪ ፓኪስታን እና ፊሊፒንስን ጨምሮ 9 ሀገሮች መካተታቸው ተገልጿል።
ስለሆነም ተጨማሪ ድጋፉ አፍሪካ ፣ እስያ እና ላቲን አሜሪካ ለሚኖሩ ሀገሮች ህመምተኞችን ለመመርመር እና ለማከም ፣ መሳሪያዎችን ለመታጠቅ ፣ የመረጃ ዘመቻዎችን ለማስጀመር እና የሰብአዊ እርዳታዎችን ለማቋቋም የሚያስችል ነው ተብሏል።
ምንጭ፡-ቢ.ቢ.ሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!