የሀገር ውስጥ ዜና

ዕጣን ተብሎ ሊሸጥ የተዘጋጀ ከ100 ከረጢት በላይ የተፈጨ እምነበረድ ተያዘ

By Meseret Awoke

August 10, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከዕጣን ጋር ተደባልቆ ሊሸጥ የተዘጋጀ ከ100 ከረጢት በላይ የተፈጨ እምነበረድ በተለያዩ ቦታዎች በህዝብ ጥቆማ ተይዟል።

በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ቀበሌ 18 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ መሰረት በአነስተኛ የቆርቆሮ ቤት ውስጥ የተቀመጠ 57 ከረጢት የተፈጨ ዕምነበረድ ፖሊስ በማግኘቱ ከቀናት በፊት ምርመራ እየተጣራ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

በተጨማሪም በዚሁ አካባቢ በተመሳሳይ በሌላ የቆርቆሮ ቤት ውስጥ ተዘጋጅቶ የተቀመጠ የተፈጨ ዕምነበረድ መኖሩ በደረሰ ጥቆማ ተጨማሪ መረጃና ማስረጃ ለማሰባሰብ ሲባል ቤቱ ታሽጎ በፖሊስ አባላት እየተጠበቀ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ትናንት ለፖሊስ በመጣ ጥቆማ መነሻነት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ዕጣን ተራ አካባቢ በተመሳሳይ ለገበያ ሊቀርብ የተዘጋጀ 52 ከረጢት በቆርቆሮ ቤት ውስጥ በብርበራ መያዙም ነው የተገለጸው፡፡

የተፈጨ ዕምነበረድን ዕጣን አስመስሎ ለመሸጥና ህብረተሰቡን ለማታለል በተፈፀመው በዚህ ህገ ወጥ ተግባር የተጠረጠረ አንድ ግለሰብ መያዙንም ከፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋልም የምርመራ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉም ነው የተነገረው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!