አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ሀገራት የበረሃ አንበጣ ወረራን በጋራ እንዲቆጣጠሩ አሳስቧል።
የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ በፈረንጆቹ ነሐሴ 9 ቀን 2023 በኬንያ ናይሮቢ ተካሂዷል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ እና የምግብ ዋስትና እጥረትን ለመከላከል በፈረንጆቹ የካቲት 9 ቀን 2020 በኢትዮጵያ የተካሄደውን 34ኛ የኢጋድ የመሪዎች እና የመንግሥታት አስቸኳይ ጉባኤ ውሳኔን በመደገፍ ነው ሚኒስትሮቹ ጥሪውን ያቀረቡት።
አባል ሀገራቱ የበረሃ አንበጣ ወረራ መቆጣጠሪያ ድርጅትን ጨምሮ ከጎረቤት ሀገራት እና ከሚመለከታቸው ኤጀንሲዎች ጋር እንዲሰሩ እና የበረሃ አንበጣን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።
እንዲሁም በቀጣናው የበረሃ አንበጣን የወረራ ሁኔታን በመተንበይ፣ በመከታተልና በመቆጣጠር ረገድ አባል ሀገራቱ አቅማቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸውም አመልክቷል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀጣይም ለኢጋድ አባል ሀገራት የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝን ለመቋቋም የሚያስችል የፋይናንስ፣ የቴክኒክ እና የሎጀስቲክስ አቅም ለመገንባት ድጋፍ እንዲያደርጉ ለልማት አጋሮቹ ጥሪ አቅርቧል።