አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደሀገር ያለውን ከፍተኛ የሳተላይት መረጃ ፍላጎት ለመመለስ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
እየቀረበ ያለውን ፍላጎት ለመመለስም በራስ አቅም ሳተላይት ከማምጠቅ በተጨማሪ በሌሎች ሀገራት ሳተላይቶች በትብብር ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ የሳተላይት ምስሎች እየተሰበሰቡ ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው ሐምሌ ወር ኢትዮጵያ ከቻይና ሳተላይቶች መረጃ የምትቀበልበትን የሳተላይት መረጃዎች መቀበያ ጣቢያ (ኖድ) ይፋ ማድረጓን በኢንስቲትዩቱ የሳተላይት ኦፕሬሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ሙካ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በኖዱ አማካኝነትም ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የሳተላይት ምስሎችን በመሰብሰብ፥ ለግብርና፣ የተፈጥሮ ሀብት ቁጥጥር፣ ትልቅ ልኬት ካርታ ሥራ፣ የተፈጥሮ አደጋ ክትትል እና ለሌሎች ሥራዎች የሚውሉ መረጃዎች እየተሰበሰቡ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ከፍተኛ (2 ሜትር) ሪዞሉሽን ያላቸው መረጃዎችን ከቻይና ሳተላይቶች ኢትዮጵያ እያገኘች መሆኗን ጠቅሰው፤ ከዚህ በተጨማሪ 5 ሜትር ሪዞሉሽን ያላቸው መረጃዎች እንደሚገኙም ገልጸዋል።
እስካሁንም የኢትዮጵያን 38 በመቶ የሚሸፍን መረጃ መሰብሰቡን ጠቅሰው፥ ትብብሩ ለአምስት ዓመት እንደሚቆይ እና በየዓመቱም የሳተላይት መረጃ ቅበላው እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።
በዚህ ኖድ አማካኝነት የሚሰበሰቡ የሳተላይት መረጃዎች የሀገሪቱን ሙሉ የቆዳ ስፋት እንደሚሸፍኑ ጠቅሰው፤ የሳተላይት መረጃዎች ግምታዊ ዋጋ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ጋና፣ ግብፅ፣ ናይጄሪያ፣ ዚምባብዌ እና ዛምቢያ የራሳቸውን ኖድ ገንብተው የሳተላይት መረጃዎችን በነፃ እየሰበሰቡ ያሉ ሀገራት ናቸው ብለዋል፡፡
ይህ ትብብር በፈረንጆቹ 2021 በ 8ኛው የቻይና-አፍሪካ ትብብር የሚኒስትሮች ጉባዔ መነሻ ሐሳብ በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት እና በቻይና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ላንድ ሳተላይት ሪሞት ሴንሲንግ አፕልኬሽን ማዕከል (LASAC) ተግባራዊ የሆነ ነው ብለዋል።
በፈረንጆቹ 2021 የብዝኀ ሳተላይት ግራውንድ መቀበያ ጣቢያ በኢትዮጵያ ተገንብቶ ከፍተኛ የምስል ጥራት ያላቸውን የሳተላይት ምስሎች ከአምስት ሳተላይቶች የመቀበል አቅም መፍጠር መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው