የሀገር ውስጥ ዜና

ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የተሰጠ ወቅታዊ መረጃ (ቁጥር- ሁለት)

By Amare Asrat

August 15, 2023

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ሰሞኑን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራዎቹን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ የሁለተኛ ዙር ምዕራፍ ሥራዎችን መጀመሩን ማስታወቁና ክልከላዎችን መጣሉ የሚታወስ ነዉ፡፡

ዛሬ ማለዳ ላይ ባደረገዉ ግምገማ፣

የሁለተኛዉ ዙር ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሥራዎች ከሞላ ጎደል እየተጠናቀቁና እየተወሰደ ባለው ርምጃ አብዛኞቹ አካባቢዎች ወደ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሱ መሆናቸዉን አረጋግጧል፡፡ በተፈጠረዉ መረጋጋትና ሰላም፣ በሁሉም አካባቢዎች ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዉይይት መጀመሩን፣ የመንግሥት፣ የግልና የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ወደ መደበኛ ሥራቸዉ እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን፣ ሕዝቡ ለመከላከያ ሠራዊታችን እያሳየ ያለው አቀባበል፣ የስንቅና የማበረታቻ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን፣ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ ያለው ፍላጎትና እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ዕዙ አረጋግጧል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ የፈጠረለትን ሰላማዊ ሁኔታ በመጠቀም አርሶ አደሩ ወደ መኸር አዝመራ ሥራዉ እየተመለሰ ነው፡፡ የግብርና ግብአቶችንም ወደየአካባቢዎቹ ለማጓጓዝ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ዕዙ በግምገማዉ አይቷል፡፡ በቀጣዮቹ ቀናት በሚወሰዱ የማጥራት ርምጃዎች የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥብቅ መመሪያ ሰጥቷል፡፡

የተጀመሩትን መደበኛ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ለማጠናከር እንዲቻል፣ ክልከላ በተደረገባቸው ስድስት የአማራ ክልል ከተሞች ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ወይንም በተለምዶ ባጃጅ በመባል የሚጠሩት ተሸከርካሪዎች አገልግሎት እንዲጀምሩ ከኅብረተሰቡ የቀረበዉን ጥያቄ ዕዙ መርምሯል፡፡

ዕዙ በከተሞቹ አጠቃላይ ሁኔታ ያደረገውን ግምገማ መሠረት በማድረግ ከነገ ነሐሴ 10 ቀን 2015፣ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ፈቅዷል፡፡

ከዚህም ጋር በማያያዝ ክልከላው ከተነሣበት ጊዜ ጀምሮ የባጃጅ ባለቤቶችና አሽካርካሪዎች የጽንፈኛ ቡድኑን አባላት፣ የዘረፉትን ንብረቶችና የትኛዉንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ከማጓጓዝ እንዲቆጠቡና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይህንን ተላልፈዉ በተገኙት ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማሕቀፍ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ አዟል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ

ነሐሴ 9 ቀን 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ