የሀገር ውስጥ ዜና

ከ11 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ይዞ የተሰወረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

By Feven Bishaw

August 15, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ11 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ይዞ የተሰወረ እና ሳይታገት ታግቻለሁ ብሎ ለአጋቾቹ 2 ሚሊየን ብር ገቢ እንዲደረግ የጠየቀ ግለሰብ ከነ ግብረአበሩ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ታግቻለሁ ብሎ በአቋራጭ ገንዘብ ለማግኘት የሞከረው የግለሰብ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ በሾፌርነት ተቀጥሮ የሚሰራ ነው፡፡

አሽከርካሪው ሐምሌ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በተሽከርካሪው የተጫነውን 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የልብስ ሳሙና ወደ መተማ ከተማ እንዲያደርስ በባለ ንብረቱ ትዕዛዝ ተሰጥቶት መነሻውን ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው አዲሱ ሚካኤል አካባቢ በማድረግ ጉዞ ይጀምራል፡፡

ነገር ግን አሽከርካሪው ወደተባለው ስፍራ ሳይሄድ ሙከጡሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደታገተ እና አጋቾቹ 2 ሚሊየን ብር ገቢ ካልተደረገላቸው እንደማይለቁት ለዚህ ወንጀል ተባባሪ በሆነው ግብረአበሩ አማካይነት ለተሽከርካሪው ባለንብረት ስልክ ማስደወሉ ተገልጿል፡፡

የግል ተበዳይም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለአውቶቡስ ተራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሁኔታውን ካሳወቁ በኋላ ፖሊስ የምርመራና የክትትል ቡድን በማቋቋም ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ጭምር በመንቀሳቀስ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቷል።

በተደረገው ክትትልም አሽከርካሪው እና 2 ሚሊየን ብር ገቢ እንዲያደርጉ ለግል ተበዳይ ስልክ ደውሎ በመንገር በወንጀሉ የተሳተፈው ግብረአበሩ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

7 ሚሊየን 600 ሺህ ብር ዋጋ አለው የተባለውን ከባድ ተሽከርካሪ ለመያዝ በተደረገው ክትትልም ከ4 ሚሊየን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለውን የልብስ ሳሙና እንደጫነ በቢሾፍቱ ከተማ ኦራ ወረዳ አሮጌው መናኸሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አጥር ጥግ ቆሞ ሊገኝ መቻሉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።