አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ተወካይና የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ሆነው ከተሾሙት ራሚዝ አላክባሮቭ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ለዋና ተወካዩ በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታና እና በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ስለ ሀገራዊ ሪፎርም ሂደት እና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ያሳካቻቸውን ውጤቶችና ያጋጠሟትን ፈተናዎች አንስተዋል።
የአካባቢ ጥበቃን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን ተግባራትም ጠቅሰዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ፥ በሽግግር ፍትህ ሂደት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን የገለጹ ሲሆን መንግስት በአገሪቱ ሰላምን ለማፅናት ቁርጠኛ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመፈረም ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ፥ የስምምነቱ አተገባበርም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የመልሶ ግንባታና የመልሶ ማቋቋም ስራውም በመልካም ሂደት ላይ እንደሚገኝና ለተግባራዊነቱም መንግስት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
አምባሳደር ምስጋኑ በሰሜኑ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ተመድ በተለያዩ ተቋማቶቹ በኩል ላደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ተቋሙ በድህረ-ግጭት ወቅት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማውሳትም ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድም ከተመድ የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ ነው ያሉት አምባሳደር ምስጋኑ ፥ ከዚህ አንጻር የተቋሙ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ተጨባጭ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑንና ለዚህም ተመድ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
በኢትዮጵያ የተመድ ዋና ተወካይ ራሚዝ አላክባሮቭ በበኩላቸው ፥ በኢትዮጵያና በተመድ መካከል የሚኖረው ሁለንተናዊ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን እንደተዘጋጁ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።