አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ከ26 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የመድኃኒት ግብዓቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀዱን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
ከ13 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የህክምና መሳሪያዎችና መገልገያዎች፣ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የንጽህና መጠበቂያዎች እንዲሁም ከ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ቶን በላይ ደኅንነቱ የተረጋገጠ ምርትና የምርት ግብዓት ወደ ሀገር ውስጥ ስለመግባቱ ተገልጿል።
በ70 የምግብ አምራች ድርጅቶችና በ18 ኮስሞቲክስ አስመጪዎች ላይ ስረዛ፣ ዕገዳና የማስጠንቀቂያ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ከ75 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው በህገወጥ መንገድ የተመረቱ የመዋቢያ ምርቶች ከውጭ ሀገራት እንዳይገቡ ማድረጉንም ነው የገለፀው።
እንዲሁም ከ41 የምግብ ምርቶች በተወሰደ 1 ሺህ 392 ናሙና 1 ሺህ 359 መስፈርቱን ሲያሟሉ÷ 26 በሂደት ላይ መሆናቸውና 8 ከደረጃ በታች ስለሆኑ ወደ ሀገር እንዳይገቡ ተደርጓል ብሏል።
በገበያ ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከደረጃ በታች የሆኑ 211 የምግብ ዓይነቶች መገኘታቸውን ነው ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለፀው።
እርምጃ ከተወሰደባቸው 242 የመድኃኒትና ሕክምና መገልገያ መሳሪያ አስመጪና አከፋፋይ ተቋማት መካከል፥ 33 ስረዛ፣ 21 ዕገዳ፣ 188 ማስጠንቀቂያ መሆኑ ተጠቅሷል።
በተደረገ የቁጥጥር ሥራ በሕገ-ወጥ ተግባራት ተሰማርተዋል በተባሉ አካላት 40 የወንጀል ክስ አቤቱታ ቀርቦ በአንዱ ላይ ውሳኔ መሰጠቱ ተጠቁሟል።
ከምዝገባ ጋር በተያያዘም፥ በአጠቃላይ ባለስልጣኑ የመዘገባቸው የምግብ ምርት ዓይነቶች 12 ሺህ 807 እንዲሁም እስካሁን 3 ሺህ 845 መድኃኒቶችን መዝግቦ የገበያ ፈቃድ መስጠቱ ነው የተመለከተው።
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!