ዓለምአቀፋዊ ዜና

በአትላንቲክ ወቅያኖስ በተከሰተ የጀልባ አደጋ 60 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁ ተገለፀ

By Mikias Ayele

August 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአትላንቲክ ወቅያኖስ ኬፕ ቬርዴ የባህር ዳርቻ አካባቢ በተከሰተ የጀልባ መገልበጥ አደጋ 60 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁ ተሰምቷል፡፡

የሴኔጋል ዜግነት እንዳላቸው የተገለፀው 100 ፍልሰተኞች ከምዕራብ አፍሪካ ተነስተው አትላንቲክ ውቅያኖስን እያቋረጡ በነበረበት ወቅት በተከሰተው የጀልባ መገልበጥ አደጋ የደረሱበት አለመታወቁ ነው የተገለፀው፡፡

ሴኔጎ የተባላውን አካባቢያዊ ሚዲያ ጠቅሶ አናዶሉ ኤጀንሲ እንደዘገበው÷ ከ100 ፍልሰተኞች ውስጥ አራት ህፃናትን ጨምሮ የ38 ሰዎችን ህይወት ማትረፍ ተችሏል።

የ7 ሰዎች አስከሬንም በአሰሳ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

ጀልባዋ በፈረንጆቹ ሐምሌ 10 ቀን 2023 ከሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር በስተሰሜን 145 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ፋስ ቦዬ ከተማ ከ100 በላይ ፍልሰተኞችን አሳፍራ በመነሳት ጉዞ ጀምራ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል።

ቀደም ሲል በሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ወደ አውሮፓ በሚወስደው የካናሪ ደሴቶች በተፈጠረ የስደተኞች ጀልባ መገልበጥ አደጋ 15 ሰዎች መሞታቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡