የሀገር ውስጥ ዜና

የፋና ላምሮት ምዕራፍ 14 ውድድር በአጸደማርያም ያረጋል አሸናፊነት ተጠናቀቀ

By Shambel Mihret

August 19, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠንካራ ፉክክር የታየበት የፋና ላምሮት የድምፃውያን የተሰጥዖ ውድድር ምዕራፍ 14 በአጸደማርያም ያረጋል አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

ላለፉት 8 ሳምንታት በዳኞችና በራሳቸው ምርጫ ሲወዳደሩ የነበሩ ተወዳዳሪዎች በዛሬው የፍጻሜ ውድድር ላይ ትንሳኤ ስለሺ፣ ትዕግስት አስማረ፣ አፀደማርያም ያረጋል እና ባምላክ ቢያድግልኝ ከኮከብ ባንድ ጋር በ3 ዙር ሙዚቃቸውን በማቅረብ ጠንካራ ፉክክር አሳይተዋል።

ከ6:00 ሰአት ጀምሮ በተካሄደው የምዕራፍ 14 የፍፃሜ ውድድር በአሸናፊነት ያጠናቀቀችው አጸደማርያም ያረጋል 400 ሺህ ብር፣ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀችው ትዕግስት አስማረ 300 ሺህ ብር፣ ሶስተኛ የወጣው በአምላክ ቢያድግልኝ 200 ሺህ ብር እንዲሁም ውድድሩን በአራተኛነት ያጠናቀቀው ትንሳኤ ስለሺ 100 ሺህ ብር ሽልማት አግኝተዋል።

ሽልማቱን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ለተወዳዳሪዎች ሽልማቱን አበርክተዋል።

በምዕራፉ በስምንተኛ ሳምንት ከውድድሩ ውጪ የሆነችው ራሄል ተሬሳ የ50 ሺህ ብር ሽልማት ስታገኝ በልዩ ሁኔታ በአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ላይ ተሳታፊ እንድትሆንም ተደርጓል።

ከ2011 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ መድረክ ያጡ ድምፃውያንን መድረክ እንዲያገኙ ያስቻለው ፋና ላምሮት በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን እያሳየ ቀጥሏል።

ፋና ላምሮት በአመት ውስጥ የአሸናፊዎች አሸናፊን ጨምሮ አራት ምዕራፎችን የሚያካሂድ ሲሆን÷ እያንዳንዱ ምዕራፍ ለዘጠኝ ሳምንታት ይቆያል።

በሶስት የተለያዩ ምዕራፎች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ በአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ላይ አንድ ላይ ይገናኛሉ።