የሀገር ውስጥ ዜና

ለገበያ እንዳይቀርብ የተከለከለ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሲሸጡ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Feven Bishaw

May 08, 2020

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለገበያ እንዳይቀርብ የተከለከለ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት 15 ሺህ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሲሸጡ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መርማሪ ሳጅን ማናስበው አላምረው እንደገለፁት ተጠርጣሪዎቹ ለገበያ እንዳይቀርብ የተከለከለ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የንግድ ፍቃድም ሆነ ከምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ህጋዊ የፈቃድ ወረቀት ሳይኖራቸው በማህበራዊ ድረ ገፅ በማስተዋወቅ እና ለሽያጭ በማቅረብ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲጠቀሙ በመሸጥ ላይ እንዳሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ገልጸዋል።