የሀገር ውስጥ ዜና

በምስራቅ አፍሪካ የሚስተዋለውን የሽብርተኝነት አደጋና ግጭት እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ

By Feven Bishaw

August 20, 2023

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ አፍሪካ የሚስተዋለውን የሽብርተኝነት አደጋና የግጭት መበራከት የቀጣናው ሀገራት በጋራ እልባት ሊያበጁለት እንደሚገባ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የፀጥታና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ገለጹ።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የፀጥታና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ÷ አልሻባብና ሌሎችም የሽብር ቡድኖች ቀጠናውን ለማወክ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጠናው ለሚስተዋለው የሽብርተኞች እንቅስቃሴ አንዱ ምክንያት በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚፈጠር የእርስ በእርስ ግጭቶችና አለመረጋጋት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የግጭት መበራከት ዘላቂ መፍትሄ በማበጀት የሽብርተኞችን አደጋ በጋራ መመከትና ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ይገባል ነው ያሉት።

ለአካባቢው አለመረጋጋት ሌላኛው ምክንያት የጂኦ-ፖለቲካ ሽኩቻ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ የቀጠናው ሀገራት ለችግሮቻቸው የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የህዝቦች ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ ሁሉም አባል ሀገራት የድርሻቸውን እንዲወጡ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡