የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታ ይፋ ሆነ

By Melaku Gedif

August 21, 2023

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቻይናው ኤፍ ኤች ኢ ሲ ኩባንያ ጋር በሽርክና የሚያስገነባው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታ ይፋ ተደርጓል፡

የከተማ አስተዳደሩ ለዚህ ፕሮጀክት የሚሆን መሬት በወቅታዊ የሊዝ ዋጋ አስልቶ ማቅረቡን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

የቻይናው ኤፍ ኤች ኢ ሲ ኩባንያ  ደግሞ ወቅቱ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ፣ ፋይናንስና ግብዓት በማቅረብ ግንባታውን  እንደሚያከናውን ተገልጿል፡፡

ጎተራ አካባቢ የሚገነባው ይህ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የሚገነባ ነው ተብሏል፡፡

በውስጡም ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚና የንግድ ዞን ፣ የትምህርት እና የባህል ዞን፣ የፋይናንስና ቢዝነስ ዞን እንዲሁም ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ዞንን እንደሚያካትት ተጠቁሟል፡፡

ፕሮጀክቱ ወደ ከተማዋ የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎችን ቁጥር በመጨመር ዓለም አቀፍ ሚናዋን እንደሚያጎላ ታምኖበታል፡፡