አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን ለማስቆም የተጀመረው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።
አቶ ኦርዲንን ጨምሮ የክልሉ ካቢኔ የጁገል ግንብ ዙሪያ የኤሌትሪክ ዝርጋታ፣ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች፣ የኢንዱስትሪ መንደር ፕሮጀክት ግንባታ፣ ከኤረር በር እስከ አውመር ቀበሌ የሚገነባው የአስፓልት መንገድን ጎብኝተዋል፡፡
ከህገ ወጥ የመሬት ወረራና ቤት ግንባታ ጋር በተያያዘ እልባት ለመስጠት እየተከናወነ ያለው ተግባር አበረታች ቢሆንም÷ አሁንም ክፍተት መኖሩን አቶ ኦርዲን በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግስትም በተያዘው በጀት ዓመት በተለይ ህገ ወጥ ቤት ግንባታን ለመከላከል በቁርጠኝነት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮም ለነዋሪው የመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚያገለግሉ መሬቶችን የማዘጋጀት ስራ ማከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት የሚፈጥሩ አካላትን ተጠያቂ ይደረጋሉም ነው ያሉት።
የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አሚና አብዱልከሪም በበኩላቸው÷ በህገ ወጥ መንገድ የተሰሩ ቤቶችን የማፍረስና መሬቱን የማስመለስ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በህገ ወጥ ቤት ግንባታ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው÷ ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!