ዓለምአቀፋዊ ዜና

ብሪታኒያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመዋጋት ትብብር እንድታደርግ ኢራቅ ጠየቀች

By Meseret Awoke

August 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪታኒያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመዋጋት ትብብር እንድታደርግ ኢራቅ ጥሪ አቀረበች፡፡

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሺዓ አል-ሱዳኒ የብሪታንያ የደህንነት ሚኒስትር ቶም ቱገንድሃትን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ከብሪታኒያ ጋር በመተባበር ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎችን፡- በተለይም ኮንትሮባንድን፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ ከአደንዛዥ እፅ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችንና የተዘረፉ ገንዘቦችን ማስመለስ እንደሚገባ ገልዋል።

በተለይም በወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦችን አሳልፎ መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ሙስና ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን የገለጹት የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር፥ ሙስናን መዋጋት ኢራን ብቻ ሣይሆን መላው የዓለም ሀገራትን የሚመለከት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ኢራቅ፥ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዲሚ እና የቀድሞ የሀገሪቱ መረጃ ኃላፊን ጨምሮ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ከሀገሪቱ የታክስ ኮሚሽን ዘርፈዋል በሚል ክስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ኢንተርፖል እርምጃ እንዲወስድ ለመጠየቅ ማቀዷንም ነው የተናገሩት።

የኢንተግሪቲ ኮሚሽኑ ዋና ዳኛ ሃይደር ሃኖን በበኩላቸው፥ በኢንተርፖል እንዲፈለጉ የተጠየቁትን ግለሰቦችን መያዝ እንደሚፈልግ አስታውቀዋል።

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር፥ በፈረንጆቹ ከ2023 እስከ 2026 መንግስት በኢራቅ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የመዋጋት ሀገራዊ ስትራቴጂ እንዲሁም ከ2023 እስከ 2025 አደንዛዥ እጽ ዝውውርን የመዋጋት ብሄራዊ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን አፅንዖት ሰጥተዋል።

ሀገራቸው አደንዛዥ እጽን እና ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋት ከፍተኛ ጥረት ማድረጓንም ነው ያነሱት፡፡

የኢራቅ መንግስት ከብሪታንያ ጋር የተደረገ የሀገር ውስጥ ሚኒስትሮች የጋራ መግለጫና የስምምነት ሰነድ ፊርማን በደስታ ይቀበላልም ብለዋል።

አክለውም ፥ ኢራቅ አይኤስን ለመዋጋት በምትወስደውን እርምጃ ብሪታኒያ የምታደርገውን ድጋፍ ማድነቃቸውን አሽራቅ አል አውሳት ዘግቧል።

የብሪታንያ ሚኒስትር ለኢራቅ የጸጥታ ኃይሎች ተጨማሪ ድጋፍ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላትም ነው የገለጹት፡፡

በመጨረሻም፥ ሁለቱ ወገኖች በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ተወያይተው፥ በፀጥታና ወታደራዊ ዘርፍ፣ ሽብርተኝነትን እንዲሁም ሙስናን በመዋጋት ረገድ ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ተስማምተዋል።

#iraq #britain #Interpol

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!