የሀገር ውስጥ ዜና

የፕሬዚዳንት ቢን ዛይድ የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ትስስር ይበልጥ ያጠናከረ ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

By Feven Bishaw

August 24, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ትስስር ይበልጥ ያጠናከረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም÷ የሚኒስቴሩን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም÷ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ትስስር ይበልጥ ያጠናከረ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅና ባህረ ሰላጤው ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ትብብር ያሸጋገረ ምዕራፍ መሆኑንም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያና በየተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል የተለያዩ ስምምነቶች መፈረማቸውን አሰታውሰው ከስምምነቶቹ መካከል የኢኮኖሚ፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የግብርና እና የትምህርት ይገኙበታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥና በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ በጋራ መስራት የሚያስችል የትብብር ፍላጎት እንዳለ በሁለቱም አገራት መሪዎች መገለጹን አምባሳደር መለስ ዓለም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የባለብዙ ወገን አራማጅ ሀገር በመሆኗ የገንቢ ገለልተኝነት የዲፕሎማሲ አቋም አንዳላትም አስረድተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነት በመፍጠር አሳታፊ የዲፕሎማሲ ትብብሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል።