የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ዛምቢያ ለጋራ ተጠቃሚነት የሚያግዙ ትስስሮችን ሊፈጥሩ ይገባል – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

By Shambel Mihret

August 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ የአፍሪካውያንን ትብብር በማጠናከር ለጋራ ተጠቃሚነት የሚያግዙ ትስስሮችን ለመፍጠር ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)ገለጹ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከዛምቢያ አምባሳደር ሮዝ ሳካላ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይታቸው የሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚነት ለማጎልበትና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች አስቻይ ግንኙነቶችን ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በዚህ ወቅት በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ የአፍሪካውያንን ትብብር በማጠናከር ለጋራ ተጠቃሚነት የሚያግዙ ትስስሮችን ለመፍጠር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ዛምቢያ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር እንዲመጣ ኃላፊነቷን እየተወጣች መሆኑን ጠቅሰው÷ኢትዮጵያም አገር በቀል የ10 ዓመት የኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራም ቀርጻ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ለመተባበር፣ ልምዶችን ለመካፈልና የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን ለማስፋት የትብብር ማዕቀፎችን ቀርጾ መተግበርና አፍሪካን የማስተሳሰር ሚናን ልንወጣ ይገባል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የዛምቢያ አምባሳደር ሮዝ ሳካላ በበኩላቸው÷አፍሪካውያን ያለንን የተፈጥሮ ሃብትና የወጣት ጉልበት በቴክኖሎጂ በማገዝ በጋራ ለመጠቀም መተባበር እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡