ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሩሲያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች

By Alemayehu Geremew

August 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ለመነጋገር በሯ ክፍት እንደሆነ የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አስታወቁ፡፡

ሰርጌ ላቭሮቭ የሩሲያን አቋም የተናገሩት በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ከሚገኘው በ“ብሪክስ” አባል ሀገራት ጉባዔ ቀጥሎ በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ እንደሆነች ነገር ግን ለማሥፈራሪያ ቦታ እንደሌላት ማስገንዘባቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

የምዕራቡ ዓለም ዲፕሎማቶች ለውይይት የሚቀመጡት ለመደማመጥ እና የጋራ አቋም ለመያዝ ሳይሆን ትዕዛዝ ለማስተላለፍ በሚመስል መልኩ ነበር ሲሉም ነው ሰርጌ ላቭሮቭ ከጋዜጠኖች ጋር በነበራቸው ቆይታ ያስረዱት፡፡

አሁንም አሜሪካ እና አጋሮቿ ተመሳሳይ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ የሚከተሉ ከሆነ ሞስኮ ለዛቻ ቦታ እንደሌላት ተናግረዋል፡፡