የሀገር ውስጥ ዜና

የጋምቤላ ክልል ያዘጋጀው የግብርና ፍኖተ-ካርታ ይፋ ሆነ

By Alemayehu Geremew

August 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የጋምቤላ ክልል ያዘጋጀው ግብርናን ማሻገር እንደሚያስችል የታመነበት ፍኖተ-ካርታ ይፋ ተደረገ፡፡

ፍኖተ ካርታው ይፋ የሆነው የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነው፡፡

ፍኖተ-ካርታው ÷ የክልሉን የግብርና ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር ተወካይ ሮድ ጋትዌች ተናግረዋል፡፡

ሠነዱ በክልሉ ያሉ መልካም ዕድሎችን፣ እየተመረቱ ያሉ የግብርና ምርቶችን አሁናዊ ሁኔታ፣ በምርት ላይ ያሉ ተግዳሮቶና መፍትሄ የያዘዘ ነውም ተብሏል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ÷ በክልሉ ያሉ በርካታ መልካም ዕድሎችን አብራርተው ÷ በፍኖተ-ካርታው ውስጥ የተካተቱትን ምክረ-ሃሳቦች በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ የክልሉን ግብርና ማሻገር ይገባል ማለታቸው ተገልጿል፡፡

የ2016 በጀት ዓመት የግብርና ሥራ ዕቅድም ከክልሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ-ካርታ ጋር የተናበበ ሊሆን እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

የፌደራል መንግስት ለፍኖተ-ካርታው ተግባራዊነት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም ቃል መግባታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ፍኖተ-ካርታውን በማዘጋጀት ረገድ ጉልኅ ሚና የነበራቸው ተቋማት እና ግለሰቦች ዕውቅናና ሽልማት ተደርጎላቸዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት መሆኑም ተነግሯል፡፡