አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ የ”ብሪክስ” አባል ሀገር መሆኗ በዓለም አቀፍ የባለ-ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረኮች ያላት ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን ያመላከተ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁማ በኢኮኖሚና ዲፕሎማሲ መስክ ያስመዘገበችው ስኬት ተደማጭነቷ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና በባለብዙ ወገን መድረኮች ተገቢውን ስፍራ ለማግኘት ከፍተኛ ሥራ መከናወኑን ቢልለኔ ሥዩም አስታውሰዋል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ እያስመዘገበች ያለው ዕድገት የዲፕሎማሲ አቅሟ እንዲጎለብት ማድረጉንም ነው የጠቆሙት፡፡
የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱም የዚሁ ማሳያ እንደሆነና ይህም ከራሷ ባለፈ የአፍሪካን ጥቅም ለማስከበር እንድትሠራ እንዲሁም በቡድኑ ውስጥ ካሉና ኢኮኖሚያቸው እያደገ ከመጡ ሀገራት ጋር በትብብር እንድታድግ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የዓለም ሀገራትና ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ጋር ትሥሥር በመፍጠር አብሮ ለማደግ ያላቸውን ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ጠቁመዋል።