አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አውሮፓ ኅብረት የአባል ሀገራቱን ቁጥር ለመጨመር መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሼል አዲስ አባል ሀገራትን ለመቀበል ሐሳብ እንደሚያቀርቡ ፋይናንሺያል ታይምስን ጠቅሶ አር ቲ ዘግቧል፡፡
“ብሪቲሽ ዴይሊ” የተሠኘው የዜና ምንጭም ፕሬዚዳንቱ በስሎቬንያ በሚያደርጉት ንግግር የሚያቀርቡትን ሐሳብ እንዳገኘ በዘገባው አስፍሯል።
እንደ መረጃው ከሆነ የአውሮፓ ኅብረት በፈረንጆቹ 2030 አዲስ ሀገራትን ለመቀበል እንዲዘጋጅ ጥሪ ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንደ ሞልዶቫ፣ አልባኒያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ሰርቢያ፣ ሰሜን መቄዶንያ እና ቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና ያሉ የአውሮፓ ኅብረት ዕጩ አባል ሀገራት በሚካፈሉበት የስሎቬኒያው መድረክ ላይ ሐሳባቸውን ይገልጻሉ ተብሎ ይጠበቃል።