አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ እና የደቡብ ኮሪያዋ ቹንቾን ከተሞች በትምህርትና ሥልጠና፣ በመሬት አስተዳደር፣ ከተማን በማዘመን፣ በከተማ ልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ እና በደቡብ ኮሪያዋ ቹንቾን ከተማ መካከል ያለውን ውል ለማደስ ዛሬ ደቡብ ኮሪያ ገብተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች ደቡብ ኮሪያ ሲደርሱም የቹንቾን ከተማ ከንቲባ ዪክ ዶንግ ሃንና ካቢኔያቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ከንቲባዋ በቆይታቸው በአዲስ አበባ እና በቹንቾን ከተሞች የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ መወያየታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በውይይታቸውም÷በትምህርትና ሥልጠና፣ በመሬት አስተዳደር፣ ከተማን በማዘመን፣ በከተማ ልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ አቻ የወጣቶች ልዑክ በቹንቾን ከተማ በመገኘት የባህልና የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበትን መድረክ ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የሁለቱን ከተሞች 19ኛ ዓመት የሁለትዮሽ ስምምነት ለማክበር በቹንቾን ከተማ ከንቲባ ዪክ ዶንግ ሃን የሚመራ የኮሪያ ወጣቶች ልዑክ በአዲስ አበባ ጉብኝት እንዲያደርግ ከንቲባ አዳነች ግብዣ አቅርበዋል፡፡