የሀገር ውስጥ ዜና

የቻይናዋ ሀርቢን ከኢትዮጵያ አቻ ከተሞች ጋር በትብብር እንደምትሠራ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

August 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናዋ ሀርቢን ከተማ በኢትዮጵያ ከሚገኙ አቻ ከተሞች ጋር በትብብር መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር ተካሄደ፡፡

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው በቻይና ሀርቢን ማዘጋጃ ቤት የውጭ ጉዳይ ፅሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ከሆኑት ዡ ጓዋንጉዌ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ቱሪዝም ፣ ባሕል እና ንግድ በትብብር መሥራት ከሚችሉባቸው ዘርፎች የሚነሱ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

ዡ ጓዋንጉዌ በበኩላቸው ማዘጋጃ ቤቱ በኢትዮጵያ ከተሞች ከሚገኙ ማዘጋጃ ቤቶች ጋር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም በመጪዎቹ ወራት ከሥራ ቡድናቸው እና ከከፍተኛ ልዑካቸው ጋር ሆነው ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ጠቁመዋል፡፡

አምባሳደር ተፈራም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የማዘጋጃ ቤቱን ጉብኝት ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኑን በመጥቀስ፥ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።