የሀገር ውስጥ ዜና

የህዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለይተን በቅደም ተከተል ለመፍታት እንሰራለን – አቶ አረጋ ከበደ

By Shambel Mihret

August 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “የህዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለይተን በቅደም ተከተል ለመፍታት እንሰራለን” ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔ በክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ በተደራጁ አራት ኮማንድ ፖስት እየተከናወኑ የሚገኙ የሰላም ማስከበር ስራዎችን አስመልክቶ ለካቢኔ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ሲቀርብ የነበረው የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት በመስተጓጎሉ በመኸር ሰብል ልማት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን አንስተዋል።

ከመሃል ሀገር ወደ ክልሉ የሚገቡ ነዳጅና ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ውጤቶች፣ ሸቀጦችና የፍጆታ ምርቶች በጸጥታ ስጋት ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ እንዳይቀርቡ ጫና መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡

የህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት ሰላም ሲረጋገጥና ወደልማት ስራ መመለስ ሲቻል መሆኑን ጠቅሰው፥ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል፡፡

የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ በሚደረገው ሒደትም ሁሉም ህዝብ ከመከላከያ ሰራዊትና ከጸጥታ መዋቅር ጎን በመሆን ተሳታፊ እንዲሆን መልዕክት ማስተላለፋቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡የመንግሥት ተቋማትን በተሟላ መንገድ ወደስራ በማስገባት በቀሪ ወራት የሚከናወኑ የትምህርት፣ የገቢና ሌሎች የልማት ስራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ ለማከናወን ርብርብ ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር መቆየት ዘላቂ መፍትሔ አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የክልሉን ሰላም በማረጋገጥና ህዝብ ቅር የተሰኘባቸውን ጥያቄዎችን በመለየት በቅደም ተከተል በመፍታት ክልሉን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማውጣት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡