አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽኅፈት ቤት ከክልልና ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽኅፈት ቤቶች ጋር “የጀጎል ቃል ኪዳን” የተሰኘ የመግባቢያ ሠነድ ተፈራረመ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ በሐረሪ ክልል ከነሐሴ 22 ቀን ጀምሮ የ2015 ዕቅድ ክንውንን ከክልልና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር ገምግሟል፡፡
ሠነዱ በፖለቲካ አቅም ግንባታ ዘርፍ በ2016 ለማከናወን የታቀዱ ዝርዝር መርሐ-ግብሮችን የያዘ ስለመሆኑ ተገልጿል።
ፓርቲው በ2016 በጀት ዓመት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት መሠራት ባለባቸው ተግባራት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ በማስቀመጥ በነገው ዕለት ያጠናቅቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
በሐረሪ እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ፣ ምክትል ዘርፍ ኃላፊው አቶ ሙሳ አሕመድ፣ የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልሀኪም ኡመርን ጨምሮ የሁሉም ክልል እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊዎች እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።