የሀገር ውስጥ ዜና

ለክልሉ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጡ አመራሮችን ወደ ፊት ለማምጣት በትኩረት እንሰራለን -የአማራ ክልል

By Feven Bishaw

September 02, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ ለሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጡ አመራሮችን በየደረጃው ወደ ፊት ለማምጣት በትኩረት እንሰራለን ሲል የአማራ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት የጸጥታ ተቋማትን ለማጠናከር የሰላምና ጸጥታ፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የሚሊሻና ማረሚያ ቤቶች ሃላፊዎችንና ምክትል ሃላፊዎችን ትናንት መሾሙ ይታወሳል።

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ መንገሻ ፈንታው(ዶ/ር) እንደገለጹት÷ አዲስ የተዋቀረውን የጸጥታው ዘርፍ ተቋማት እርስ በእርስና ከጸጥታ ምክር ቤቱ አባላት ጋር የመተዋወቅ፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን የመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

በአዲስ መልክ መልሶ በተዋቀሩት የጸጥታ ተቋማትም እስከ ወረዳና ቀበሌ ያለውን መዋቅራቸውን እንደገና በማደራጀት በሰላምና ደህንነት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንሰራለን በማለት ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ በተለይም ለክልሉ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጡ አመራሮችን በየደረጃው ወደ ፊት ለማምጣት በትኩረት እንሰራለን መባሉንም መንገሻ(ዶ/ር) አስታውቀዋል።

የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት የአማራ ክልልን ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በትብብር በመስራት አሁን የሚታየውን የሰላም መሻሻል ማስቀጠል እንደሚገባ መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የክልሉ የጸጥታ ተቋማት በቀጣይ ለሚያከናውኑት የሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ተግባራት የመስተዳድር ምክር ቤቱ መደገፍ የሚገባውን ለይቶ በማቅረብ መዋቅሩ ፈጥኖ ወደ ስራ እንዲገባ እንደሚደረግም ተገልጿል።