አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኩዌት የሕክምና ቡድን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ነጻ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ዛሬ መስጠት ጀመረ።
በነጻ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቱ 200 የሚሆኑ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።
የኩዌት የቀዶ ሕክምና ቡድን አማካሪና አስተባባሪ ዶክተር ሂሻም ቡረስቅ እንደገለጹት÷ የሕክምና ቡድኑ 20 ዶክተሮች፣ 11 ነርሶችና 3 የቴክኒክ ባለሙያዎችን ያካተተ ነው።
ቡድኑ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ጋር በመተባባር ከዛሬ ጀምሮ በሚሰጠው ነጻ አገልግሎት ከጠቅላላ ቀዶ ሕክምና እስከ እስፔሻሊቲ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የሕክምና አገልግሎት ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ውለታው ጫኔ ÷ ለህክምና ቡድኑ በቂ የቀዶ ሕክምና ክፍሎች ተዘጋጅተው ሥራውን በአግባቡ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው ይህም የኮሌጁን የሚሰራውን ሥራ ይደግፋል ብለዋል፡፡
ከሕክምና ቡድኑ የእውቀትና የክህሎት ልምድ ልውውጥ ለማድረግ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው በቀጣይም ግንኙነቱን ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።