አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቱርኩ አቻቸው ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የዩክሬንን የእህል ስምምነት ማደስ በሚቻልበት ዙሪያ መክረዋል፡፡
በዓለም ላይ ቁልፍ የግብርና አምራች የሆኑት ሩሲያ እና ዩክሬን በስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ የሱፍ አበባን ጨምሮ ሌሎች ምርቶች የሚያመርቱ ዋና ተዋናዮች ናቸው።
ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የእህል ምርቶች ከዩክሬን ወደ ዓለም ገበያ በጥቁር ባህር በኩል ለማድረስና የዓለምን የምግብ አቅርቦት ቀውስን ለማቃለል ያለመ ስምምነት ደርሰው ነበር።
ሆኖም ሞስኮ ስምምነቱን በሐምሌ ወር ማቋረጧ የሚታወስ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ፕሬዚዳንት ፑቲንን በማሳመን ረገድ ትልቅ ሚና የተጫወቱት ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን እና ተመድ አሁንም ፑቲንን ወደ ስምምነቱ እንዲመለሱ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።
ይህን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ፑቲን እና የቱርክ አቻቸው ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ከዩክሬን በጥቁር ባህር በኩል የሚደረጉ የእህል ማጓጓዝ ስራዎችን በተመለከተ የፑቲን መኖሪያ በሚገኝበት ሶቺ ዛሬ ተገናኝተው መክረዋል፡፡
በመሪዎች መካከል በተደረገው ውይይት የእህል ስምምነቱ ዋና ርዕሰ ጉዳይ እንደነበር የቱርኩ መሪ ተናግረዋል፡፡
ኤርዶሃን በንግግራቸው፥ “ዓለም እህል የሚጓጓዝበት ኮሪደር ላይ ትኩረት አድርጓል” ሲሉ የጉዳዩን ትልቅነት ጠቁመዋል፡፡
የሩሲያው መሪ በበኩላቸው ፥ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለመደራደር ዝግጁ ነን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የተቋረጠው ስምምነት ዓለም አቀፍ ገበያው ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን የገለጹት ኤርዶሃን ፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ መላክ ቢቻልም የመርከብና የኢንሹራንስ እገዳዎች እንቅፋት መፍጠራቸውን አመላክተዋል፡፡
ምንጭ፡- ዩሮ ኒውስ እና ሬውተርስ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!