የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ላይ እንዲሰሩ 1 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ይፋ ሆነ

By Alemayehu Geremew

September 05, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ወጣቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መፍትሄዎችን እንዲሹ ያስችላቸው ዘንድ የ140 ቢሊየን የኬንያ ሽልንግ (1 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ) ድጋፍ ይፋ ሆነ፡፡

ድጋፉን ይፋ ያደረገው የአፍሪካ ልማት ባንክ÷ ገንዘቡን ከዓለምአቀፉ “ግሎባል ሴንተር ኦን አዳፕቴሽን” (ጂሲኤ) እንዳገኘ ዘስታር ዘግቧል፡፡

የገንዘብ ድጋፉን በተመለከተ ያስረዱት የባንኩ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አዴሲና÷ ወጣቶች በግብርና፣ በኃይል፣ በውሃ አጠቃቀም፣ በንፅህና አጠባበቅና በመሳሰሉት ዘርፎች አዳዲስ ፈጠራዎችን ዕውን እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አፍሪካ በየዓመቱ ከ5 ቢሊየን እስከ 15 ቢሊየን ዶላር እንደምታጣና በዓለምአቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በካይ ጋዝ በመልቀቅ ያላት ድርሻ ግን ሦስት በመቶ ብቻ መሆኑን አንስተዋል፡፡