አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በአፍሪካ አህጉር ለሚከናወኑ አረንጓዴ የኃይል አማራጭ ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚውል የ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ይፋ አድርጋለች፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚመክረውን 28ኛው የተመድ ጉባዔ (ኮፕ28) ከፈረንጆቹ ሕዳር 30 እስከ ታኅሣሥ 12 ቀን 2023 የምታስተናግደው የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በአፍሪካ የሚካሄደውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እየደገፈች ትገኛለች።
አሁን ይፋ ያደረገችው የ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አፍሪካ የምታካሂደውን የአረንጓዴ ኃይል አማራጮች ፕሮጀክት ግንባታ ያፋጥናል ተብሎ እንደሚጠበቅም በሻራ መጽሔት ያወጣው ዘገባ አመልክቷል።
የገንዘብ ድጋፉ በአቡ ዳቢው አረንጓዴ የኃይል አማራጭ ኩባንያ ማስዳር፣ በአቡ ዳቢ ፈንድ ለልማት፣ በኤቲሃድ ክሬዲት ኢንሹራንስ እንዲሁም ዱባይ ላይ በተመሰረተው የታዳሽ ኃይል ኩባንያ ኤ.ኤም.ኢ.ኤ ፓወር ይሸፈናል ተብሏል፡፡
ድጋፉ በአፍሪካ የሚገኙ ማናቸውንም ሀገራት የሚመለከት ሲሆን÷ ግልጽ የሆነ ወደ አረንጓዴ የኃይል አማራጭ የሚደረግ የሽግግር ሥልት፣ የቁጥጥር ማዕቀፍ እንዲሁም አቅርቦትና ፍላጎትን ያማከለ የተጣጣመ የመሠረተ-ልማት ማስተር ፕላን ያላቸው ሀገራት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ተብሏል።