የሀገር ውስጥ ዜና

ስናገለግል የሀገራችንን ብሩሀ ተስፋ እያሰብን ይሁን – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

September 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ስናገለግል የሀገራችንን ብሩሀ ተስፋ እያሰብን ይሁን ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጳጉሜን 1 የአገልጋይነት ቀን በመላ ሀገሪቱ እየተከበረ ነው፡፡

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የአገልጋይነት ቀንን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ማገልገል ክብር ነው፤ እንደ ኢትዮጵያ በብዙ ተስፋና ፈተና ያለች ሀገርን ማገልገል ደግሞ ድርብ ክብር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

“በመላው ሀገራችን የዛሬውን ቀን ስናክብር ለሀገራችን በየተሰማራንበት ዘርፍ ውጤታማ የሆነ አገልግሎት በመስጠት የራሳችንን ዐሻራ እያሳረፍን መሆናችንን በማመን ሊሆን ይገባል” ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የመንግስት ሰራተኞች አሏት፤ ይህ ቁጥር ቀላል የማይባሉ ሀገራት የህዝብ ቁጥር ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

የአገልግሎት አሰጣጣችንን በማሻሻል በቁጥራችን ልክ የሚገባንን ኃላፊነት ከተወጣን ÷ በብዙ መልኩ ለነገው ትውልድ መንገድ በመጥረግ ጉልህ ዐሻራችንን እያስቀምጥን መሆኑን ልንጠራጠር አይገባም ብለዋል በጽሑፋቸው፡፡

የኢትዮጵያ ልማት እና ቀጣይ እድገት ብሎም የሰላም መሰረት አገልገሎት አሰጣጣችን ያለው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢኮኖሚ እድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ፈጣን የሆነ አገልግሎት መስጠት የግድ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን ልንርሳው የማይገባ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በብዙ ውስጣዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች እየተፈተነ በዓለም በፈጣን እድገት ላይ ካሉ ሀገራት ተርታ የሚመደብ ነው ብለዋል፡፡

በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች በቀጣይ ሙሉ ፍሬ እንዲያፈሩ የአገልገሎት አሰጣጥ ማሻሻያወች እና የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያዎች ተግባራት በመንግስት በኩል እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

“እነዚህ ጅምር የለውጥ ተግባራት በሙሉ ፍሬ ለሕዝቡ ደርሰው በዘላቂነት ችግሩ እንዲፈታ እኔ በተሰማራሁበት መስክ፣ በያዝኩት የስራ መደብ የሚጠበቅብኝን ሃላፊነት እየተወጣሁ ነኝ? ብሎ መጠየቅ ከሁላችንም የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው “ሲሉም አመላክተዋል፡፡

“በትብብር እና በጋራ መንፈስ ችግራችንን እየፈታን፣ አገልገሎት አሰጣጣችንን እያዘመን ወደ ፊት ከተራመድን የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረጋችን አይቀሬ ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡