የሀገር ውስጥ ዜና

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገለጸ

By Melaku Gedif

September 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአዲስ ዓመት በዓል የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እንዲደርሱ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮው ሃላፊ ገሌቦ ጎልቶሞ÷ ለዘመን መለወጫ በዓል የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

በእሑድ ገበያ፣ በህብረት ስራ ማህበራት እና በዩኒየኖች የበዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረጉ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

የምግብ ዘይት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች እየተሰራጨ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሥኳር አቅርቦት በተመለከተም ለበዓል ወቅት ፍላጎት አንጻር 16 በመቶ የሚሆነው ብቻ ገበያ ላይ መዋሉን አስረድተዋል፡፡

ለበዓሉ የሚውሉ የእርድ እንስሳት ለገበያ እንዲቀርቡም ከአጎራባች ክልሎች ጋር ትስስር መፈጠሩን ሃላፊው አብራርተዋል፡፡

በበዓል ገበያ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር እና ባዕድ ነገሮችን በሚቀላቀሉ ነጋዴዎች ላይ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

ማህበረሰቡም በመሰል ህገ ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ሲመለከት አቅራቢያ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በመላኩ ገድፍ