ዓለምአቀፋዊ ዜና

በሞሮኮ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ የሟቾች ቁጥር  ከ2ሺህ በላይ  ደረሰ

By Feven Bishaw

September 10, 2023

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞሮኮ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ የሟቾች ቁጥር ከ2ሺህ በላይ መድረሱ ተነገረ፡፡

አርብ ምሽት በማዕከላዊ ሞሮኮ በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 8 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ ይታወቃል፡፡

በዚህም እስካሁን የሟቾች ቁጥር ከ2ሺህ መብለጡ ነው የተነገረው፡፡

ከ1ሺህ 400 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ነው የሞሮኮ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ንጉስ መሀመድ ስድስተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋውን ተከትሎ የሶስት ቀናት ብሄራዊ ሀዘን አውጀዋል።

ከአደጋው ለተረፉት ሰዎች መጠለያ፣ ምግብ እና ሌሎች እርዳታዎች እንዲደረግላቸው አዘዋል።

አደጋው  በተከሰተበት አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች መሰል አደጋ በድጋሚ ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት አካባቢውን ለቀው እየወጡ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሞሮኮ መንግስት ዜጎችን ከአደጋው ለማዳን የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ስፔን ፣ ፈረንሳይ እና እስራኤልን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ዝግጁነታቸውን እየገለፁ ነው።

ጎረቤት አልጄሪያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሞሮኮ ጋር የሻከረ ግንኙነት ቢኖራትም አሁን ግን የአየር ክልሏን ወደ ሞሮኮ ለሰብአዊ በረራዎች እየከፈተች ነው ተብሏል።