አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ስፔን፣ እንግሊዝ፣ ኳታር እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ያቀረቡትን የነፍሥ አድን ስራ ሠራተኛ ወደ ሞሮኮ የመላክ ጥያቄ ሞሮኮ እንደምትቀበለው አስታወቀች፡፡
የሞሮኮ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት ጥያቄያቸውን እንደተቀበለው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መግለጫው ከሀገራቱ የተላኩትን የፍለጋ እና የነፍሥ አድን ሠራተኞች ከሀገሪቷ የፍለጋ እና የነፍሥ አድን ሠራተኞች ጋር በማቀናጀት እንደሚሠሩ ማመላከቱን አናዶሉ ዘግቧል፡፡
ከሀገራቱ የተላኩት ቡድኖች ሞሮኮ የገቡ ሲሆን ፥ ከሌሎች ወዳጅ ሀገራትም የሚደረጉ ድጋፎችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ እንቀበላለን ብሏል።
በተያያዘ መረጃ የቻይና ቀይ መስቀል ማኅበር ለሞሮኮ ቀይ ጨረቃ 200 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለአስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግም ለሞሮኮ ህዝብና ለሀገሪቱ ንጉስ መሐመድ ሥድስተኛ በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቷ የሚገኙ ቻይናውያን የሕክምና ባለሙያዎችም አደጋው ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ተጎጂዎችን በንቃት እየረዱ መሆናቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን አስነብቧል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽንም በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የ1 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ በአባል ሀገራቱ ሥም አስታውቋል፡፡
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ኅብረቱ በማናቸውም አሥፈላጊ እገዛዎች ሁሉ ከሞሮኮ ሕዝብ እና መንግስት ጎን መቆሙን በርናማ የተሰኘው የጀርመን የዜና ምንጭ ዘግቧል፡፡
የሟቾች ቁጥር 2 ሺህ 500 ማለፉንና ጉዳት የደረሰባቸውም ከ2 ሺህ 421 በላይ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
አርብ ማምሻውን በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 8 የተለካ ርዕደ መሬት አደጋ በሞሮኮ ከደረሰ በኋላ የተለያዩ ሀገራት አብሮነታቸውን እያሳዩ ነው፡፡