አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንድ የ264 ቢሊየን ዶላር የኢኮኖሚ መታደጊያ ማዕቀፍ ይፋ አደረገች።
ማዕቀፉ ኮሮና ቫይረስ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ያለመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ተናግረዋል።
የአሁኑ የመንግስት እርምጃ በኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ ሳቢያ የንግድ እንቅስቃሴያቸው የተጎዳባቸውንና ስራቸውን ያጡ የሃገሬው ዜጎችን ለመደጎም ያለመ ነው ተብሏል።
በዋናነትም በመሬት፣ በቀን ሰራተኞች፣ የገንዘብ ፍሰት እና ህግና ደንቦች ላይ ትኩረቱን ያደርጋልም ነው ያሉት።
እርምጃው በአነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ለተሰማሩ እና ገበሬዎች ድጋፍ ለማድረግ ያስችላልም ነው የተባለው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የተደነገገው የእንቅስቃሴ ክልከላ ለተጨማሪ ጊዜ ሊራዘም እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተዋል።
በህንድ የዜጎች እንቅስቃሴ ከፈረንጆቹ መጋቢት 25 ጀምሮ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ መታገዱ ይታወሳል።
በዚህ ሳቢያ በተለይም የቀን ሰራተኞችና በአነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚተዳደሩ ዜጎች መጎዳታቸው ይነገራል።
በርካቶችም የናሬንድራ ሞዲ መንግስት ፈጣን እርምጃ አልወሰደም በማለት ወቀሳ ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ