የሀገር ውስጥ ዜና

የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ለተፋሰሱ ሀገራት በቂ የውሃ መጠን እንዲያልፍ በማድረግ የተከናወነ ነው – ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)

By Meseret Awoke

September 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ለታችኛው ተፋሰሱ ሀገራት በቂ የውሃ መጠን እንዲያልፍ በማድረግ መከናወኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪና የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ገለጹ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት ማብሰራቸው ይታወሳል።

የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፥ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዳይጀመር በርካታ ጫናዎች ሲደረጉ እንደነበር አንስተዋል።

ግድቡ ግንባታው ከተጀመረ በኋላ የነበሩ ፈተናዎችን ኢትዮጵያ በጽናት ማለፏን በማንሳትም፥ የግድቡ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት መጠናቀቅ የነበረውን ጫና ሙሉ በሙሉ የቀለበሰ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በተለይም በዲፕሎማሲው መስክ ሰፊ ዘመቻ ሲደረግ እንደነበር በመጥቀስ ኢትዮጵያ በያዘችው እቅድ መሰረት የግድቡን የውሃ ሙሌት በማጠናቀቅ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል አስመዝግባበታለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከግል ጥቅም ይልቅ ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም እና ለቀጣዩ ትውልድ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያነሱት ያዕቆብ (ዶ/ር) ፥ ይህንንም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማሳየቱን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያውያን ችግሮችን ተቋቁመው በጥሪታቸው እየገነቡት ያለው ይህ ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ግድብ አሁን ፍሬው መታየት ጀምሯል ነው ያሉት።

የግድቡ ውሃ ሙሌት መጠናቀቅም የህዝቡ የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የእውቀት አስተዋጽዖና የጸሎት ትጋት ውጤት እንደሆነ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

አራተኛውና የመጨረሻው የውሃ ሙሌትም ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በቂ የውሃ መጠን እንዲያልፍ በማድረግ መከናወኑን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የሚገኝ የተፈጥሮ ሃብትን የመጠቀም መብት እንዳላት በሚገባ መገንዘብ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።

በቀጣይ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮችም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና የወደፊቱን ትውልድ የልማት መብት የሚያስከብር ስምምነት እንዲኖር በጥንቃቄ መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!