አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ2016 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው “በፈጣሪ ቸርነት 2015ን አልፈን ወደ አዲሱ ዘመን ደርሰናል ፤ ኢትዮጵያም በውጣ ውረድ ውስጥ እያሸነፈች ተጉዛለች” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ጽኑ መርኅ፣ ብርቱ ሕዝብና የማይሸነፍ አምላክ ስላለን እዚህ ደርሰናል” ሲሉም ነው የገለጹት።
“ብዙ ነገሮችን አሳክተናል ፤ አያሌ ፈተናዎችን በድል ተወጥተናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እልፍ መሰናክሎች ቢደረደሩም ጠንካራ መሠረት ሆነውን አልፈዋልም ብለዋል በመልዕክታቸው።
“የተሳኩልን ሁሉ የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ውጤቶች ናቸው፤ የተፈተንባቸው ደግሞ በመለያየት የተነሣ የመጡ ናቸው” ሲሉም ገልጸዋል።
አያይዘውም “በቀጣዩ ዓመት ፈተናዎቻችን እጅግ ቀንሰው፤ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ከአልማዝ ጠንክሮ፤ የኢትዮጵያን ሠላምና ደኅንነት በጽኑ መሠረት ላይ እናጸናዋለንም” ብለዋል።
የኢትዮጵያን ልማትና ብልጽግና ወደሚመጥናት ደረጃ እናሻግራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ብልጽግና ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡