የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲሱ ዓመት በተለያዩ መስኮች የተመዘገቡ ድሎች እንዲቀጥሉና ህፀጾች እንዲታረሙ በከፍተኛ ትጋት ይሰራል- አቶ አደም ፋራህ

By Melaku Gedif

September 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲሱ ዓመት በተለያዩ መስኮች የተመዘገቡ ድሎች እንዲቀጥሉና የታዩ ህፀጾች እንዲታረሙ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም ፋራህ የ2016 አዲስ ዓመትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የመልዕክታቸው ሙሉ ቃልም እንደሚከተለው ቀርቧል ፡-

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፣ የተከበራችሁ የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች፣ የተከበራችሁ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ በተለያየ የስራ መስክ ተሰማርታችሁ ሌት ከቀን የምትለፉ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለአዲሱ አመት በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውሀ ሙሌት ባጠናቀቅንበት ማግስት ላይ ሆኜ ይህን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ሳስተላልፍ ደስታዬ ወደር የለውም።

አዲስ ብለን የተቀበልነው አመት በወቅት እና በጊዜ ቅይይር ዛሬ አሮጌ ሆኖ በአዲስ የተሻለ እና ተስፋን ባዘለ አመት ሊቀየር የሰአታት እድሜ በቀሩት በዚህ ጊዜ ላይ ሀገራችን እና ህዝቦቿ ትልቅ ተስፋን ሰንቀው አዲሱ አመት ይዞት የሚመጣውን በረከት ለመቋደስ ጓጉተው እየጠበቁ ነው።

ያሳለፍነው አመት ምንም በአሮጌነት ተፈርጆ በአዲስ የሚተካ ቢሆንም እንደ ሀገር ለብልጽግና ጉዟችን ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ያስመዘገብንበት አመት ነበር።

በሰላሙ ረገድ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የገጠመንን ጦርነት በድርድር የቋጨንበት፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የታዩ ግጭቶችን በንግግርና በድርድር ለመፍታት ሰፊ ስራ የሰራንበት፣ በርካታ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ወደ ቦታቸው የመለስንበት፣ የተስተጓጎሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን መልስን ያስጀመርንበት እንዲሁም ሀገረ መንግስቱን የሚፈታተኑ መሰረታዊ ጉዳዮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችለን አካታች አገራዊ ምክክር እንዲሳካ ምቹ ሁኔታ የፈጠርንበት የስኬት አመት ነበር።

በተመሳሳይም በ2015 ዓ.ም በኢኮኖሚው ዘርፍ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ የኢኮኖሚው ስብራቶችን ለመጠገናንና ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመፍታት የሚያስችሉ ስኬቶች በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ፣ ወዘተ በማስመዝገብ ሀገራችንን እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ወቅት በዓለማችን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ካስመዘገቡ ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ከመቻላችንም በተጨማሪ የኢኮኖሚ እድገቱን ጤናማነት፣ ቀጣይነትና ዘላቂነት ለማስጠበቅም ሀገራዊ አቅምን አሟጦ ለመጠቀምና አዳዲስ ሀብቶችን ለመፍጠር የሚያስችሉ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ፡፡

ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ በምግብ እራሳችንን ለመቻልና ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመቋቋም የያዝነውን ውጥን ከማሳካት አኳያ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ ሀገር መላክ የቻልንበት ውጤት ነው፡፡ በተጨማሪም የቡና፣ የሩዝ፣ የበቆሎ፣ የጥራጥሬ፣ የአቮካዶና የመሳሰሉ ምርቶች ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል፡፡

በዲፕሎማሲው ረገድም ሀገራችን በተፈጠሩ ውስጣዊ ግጭቶች ምክንያት ስሟ እንዲያድፍ ያደረጉ ህፀፆች ለማረምና ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር ሰፊ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በተለይም የብሪክስ ሀገራት ጥምረትን መቀላቀል ከቻሉ ስድስት ሀገራት አንዷ መሆን መቻሏ የዲፕሎማሲ ጥረቶቻችን ውጤታማነት የሚያሳይ ታሪካዊ ስኬት ነው፡፡

በማህበራዊ ዘርፍም በስነ ምግባር የታነፀ ጤናማና አምራች ትውልድ ከመፍጠር አንፃር ጠንካራ መሰረት የሚጥሉ ስኬታማ ተግባራት በትምህርት፣ በጤና ጥበቃና በመሳሰሉት ዘርፎች ተከናውነዋል፡፡ ከተለያዩ ዘርፎች ከፍ ብሎ የተዘረዘሩት ለአብነት የተነሱ እንጂ እንደ ሀገር ያሰመዘገብነው ድል ተቆጥሮ የሚያልቅ አይደለም። በየቀኑ የሚመረቁ ፕሮጀክቶች፣ በሰው ተኮር ፖሊሲዎቻችን የተደፈኑ ቀዳዳዎች እልፍ አእላፍ በመሆናቸው እንዲህ በቀላሉ መግለፅ አይቻልም፡፡

እንደ ብልፅግና ፓርቲ በአሮጌው አመት በተለያዩ መስኮች የተመዘገቡ ድሎች እንዲቀጥሉ እንዲሁም የታዩ ህፀፆች እንዲታረሙ ከፊታችን ባለው አዲስ አመት በከፍተኛ ትጋት እና የኃላፊነት ስሜት የምንንቀሳቀስበት አመት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለኝም።

ዜጎች በየአከባቢያቸው የሚያነሷቸው ችግሮች እንዲቀረፉ፣ የተጎዱ የትስስር ድልድዮች እንዲጠገኑ፣ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ ፍትሓዊነት፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነት/እህተማማችነት እንዲጠናከር እና ሀገራችን በህብረ ብሔራዊ አንድነት ሸማ ደምቃ እንድትታይ ለማድረግ ያለመታከት እንደምንንቀሳቀስ ልገልፅላችሁ እወዳለሁ።

ባሳለፍናቸው የጷጉሜ 6 ቀናት እንዳመላከትነው በአዲሱ አመት የኢትዮጵያ እና የህዝቦቿ አብሮነትና አምድነት እንዲጠናከር፣ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆነው የአምራችነት አቅማችን እንዲጎለበት፣ በመስዋአትነት ፀንታ የቆመችው ውድ ሀገራችንን በአርበኝነት ስሜት በላባችን ለማጽናት፣ የነገው ትውልድ በተስፋ እና በብርሀን ይሞላ ዘንድ በጎነት ባህል ሆኖ መገለጫነቱ እንዲጎላ ያላሰለሰ ጥረት የምናደርግ ይሆናል።

ያለ ህዝብ ድጋፍ ምንም ብንለፋ ምንም ብንደክም ፍሬ አይኖርም እና ውድ ኢትዮጵያውያን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ጉድለታችንን እየደፈናችሁ እና ለሀገራችን ሁለንተናዊ ብልፅግና የድርሻችሁን እየተወጣችሁ ከጎናችን እንደምትቆሙ ምንም ጥርጥር የለኝም።

በተለይም ለሀገራችን የብልፅግና ጉዞ እንቅፋት የሆኑትን የጽንፈኝነት አመለካከቶችና ተግባራትን በትብብርና በአንድነት መንፈስ ለማረምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት ውስጥ አብሮነታችሁ እንደማይለየን በመተማመን መጪው አዲስ አመት የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ እና የብልፅግና እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቴን ለመግለፅ እወዳለው።

መልካም አዲስ አመት

አደም ፋራህ

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፅ/ቤት ኃላፊ