አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ መርሐ ግብር ጋር በመተባባር በ2016 ዓ.ም ዲጂታል የተማሪዎች መለያ ስርዓት (የተማሪ መታወቂያ) ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ ሚኒስቴሩ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የዲጂታል መታወቂያ ስርዓትን መደበኛ የተማሪዎች መለያ አድርጎ ለመተግበር መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
ይህ ተነሳሽነት ኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፉን ዲጂታል ለማድረግና ለማዘመን በምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ወቅት ላይ የተደረገ ነው ብለዋል።
የዲጂታል መታወቂያው ጥቅም ላይ መዋሉ የተማሪዎችን ማንነት በወጥነት መለየት የሚያስችል ስርዓት ማቋቋም ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
በሁሉም የትምህርት ተቋማት አበይት የማንነት ማረጋገጫ ስርዓት ሆኖ ከማገልገል ባለፈ የአሰራር ድግግሞሽን በመቀነስና በተማሪዎች የትምህርት ሰነዶች መካከል አንድነትና ቅንጅትን የሚያጠናክር ስለመሆኑም አስገንዝበዋል፡፡
የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት የግል መረጃን የማስቀመጥና የመጠቀም ደህንነትን በእጅጉ የሚጨምርና ስጋቶችን በመቀነስ ረገድ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
እንዲሁም በትምህርት ተቋማት አስተዳደራዊ ኃላፊነቶችን በተለይም እንደ የተማሪ ቅበላ፣ ፈተናና የማህደር አስተዳደር የመሳሰሉት ስራዎች የተሳለጠ አካሄድ እንዲከተሉ ያስችላል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ይህም በፋይዳ ላይ የተመሰረተ የፈቃድ አሰጣጥ እና ብሄራዊ ፈተናዎች በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ እና ምቹ በሆነ መልኩ እንዲደርሱ በሚያስችሉ ቁልፍ ተግባራት ላይ እንደሚንፀባረቅ ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በ 2016 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባን ለመጀመር ሁለቱም ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ተቋማት ውስጥ የተቀናጁ ተግባራትን ያከናውናሉ ነው የተባለው፡፡
ከዚህ ቀደም የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችን የሙከራ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ሂደት በቀልጣፋነት እና በውጤታማነት መካሄዱ ይታወሳል፡፡