የሀገር ውስጥ ዜና

የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በማተምና ጥቁር ገበያ በማስፋፋት በተጠረጠሩት ግለሰቦች ላይ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተፈቀደ

By Alemayehu Geremew

September 13, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በማተምና ጥቁር ገበያን በማስፋፋት ወንጀል በተጠረጠሩ 12 ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ እንዲችል ለፖሊስ 14 ቀናት ፈቀደ።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ÷ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮውን ለፖሊስ የፈቀደው የተሰሩና ቀሪ የምርመራ ስራዎችን እንዲሁም የተጠርጣሪዎችን የመከራከሪያ ነጥብ መርምሮ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ የፀሐይ ሪል ስቴት ጀነራል ማናጀር ኪያ ዦንግን ጨምሮ ዘጠኝ የውጭ ሀገር ዜጎች እና ሦስት ኢትዮጵያውያን ናቸው።

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ÷ ተጠርጣሪዎቹ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በማተምና ጥቁር ገበያን በማስፋፋት ወንጀል መጠርጠራቸውን፣ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት የተለያዩ የውጭ ሀገር ገንዘብ የሚታተምባቸው ማተሚያ ማሽኖች እና ለግብዓት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች እንዲሁም በርካታ ዩሮ፣ የአሜሪካን ዶላርና የሌሎች ሀገራት ገንዘቦች መያዙን ተከትሎ የምርመራ ስራ መጀመሩን መግለጹ ይታወሳል።

በዛሬው ቀጠሮ ደግሞ÷ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጡት የ12 ቀናት የምርመራ ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን ማከናወኑን ለተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።

ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወንም ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠውም ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ÷ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ውስጥ የተጠርጣሪዎችን ተሳትፎ ለይቶ መቅረብ ሲገባው ለይቶ ባልቀረበበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁ ተገቢነት እንደሌለው በመግለጽ የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲፈቀድ በመጠየቅ ተከራክረዋል።

የፀሐይ ሪል ስቴት ጀነራል ማናጀር ኪያ ዦንግን የተባሉት ተጠርጣሪ ÷ ባጋጠማቸው የጤና እክል በቂ ሕክምና እንዲያገኙ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ÷ ተሳትፏቸውን በሚመለከት ከወንጀል ድርጊት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ብርበራዎች መቀጠላቸውን በመጥቀስ ቀሪ ምርመራውን አከናውኖ ተሳትፎ ደረጃን ለይቶ እንደሚያቀርብ ገልጿል።

የወንጀል ድርጊቱ ሀገርን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ተግባር መሆኑን የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ በመቃወም ተከራክሯል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ÷ ተጠርጣሪዎች ላይ ከቀሪ ስራ አንጻር ተጨማሪ የማጣሪያ ምርመራ መደረግ እንዳለበት በማመን የዋስትና ጥያቄያቸውን ለጊዜው ውድቅ በማድረግ ፖሊስ የምርመራ ስራውን አከናውኖ እንዲቀርብ 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ