አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የምርት ዘመን የማንም ቦታ ቢሆን ሳይታረስ ጾም የሚያድር መሬት እንደማይኖር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ኮቪድ19 በምግብ ዋስትና ላይ ያለው ተፅዕኖ እና የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ሊያስከትል በሚችለው ጉዳት ላይ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ በክረምቱ ወራት በሁለቱ ችግሮች ሳቢያ ተጨማሪ 15 ሚሊየን ሰዎች ድጋፍ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ይጠበቃል ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም ምርት ሊቀንስ እና ከውጭ የሚገባ ስንዴ በላኪ ሃገራት ላይ በሚፈጠር ችግር ሳቢያ ላይኖር ይችላልም ነው የተባለው።
የሚፈጠረውን የምርት ጉድለት ለመሙላትም ክልሎች እያንዳንዱ የሚታረስ መሬት የባለቤትነት ጥያቄ ቢኖርበት እንኳን እንዲታረስ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
መሬቱን የያዙ ሰዎች በቅድሚያ እንዲያመርቱ ይደረጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማያመርቱ ከሆነ ግን በቶሎ ወደ ስራ እንዲገባ መደረግ አለበት ብለዋል።
በዚህም በመኸሩ የሚመረተው መደበኛ ምርት እንደተጠበቀ ሆኖ በዋና ዋና ሰብሎች ላይ ተጨማሪ 40 ሚሊየን ኩንታል ለማምረት መታቀዱም ተነስቷል።
አበባን ጨምሮ በአትክልትና ፍራፍሬ ደግሞ ተጨማሪ 50 ሚሊየን ኩንታል ለማምረት ቅድመ ዝግጅት መደረግ እንዳለበትም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከገጠማት የትኛውም ችግር ለመውጣት ጠላትን መግደል፣ ራስን ማዳን፣ ሃገርን እና ህዝብን መታደግ የዚህ አመት መሪ ሃሳብ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በአላዛር ታደለ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።