የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮ-ኳታር የፓርላማ ዲፕሎማሲ ወዳጅነት ቡድን ከኳታር አምባሳደር ጋር መከረ

By Feven Bishaw

September 15, 2023

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ኳታር የፓርላማ ዲፕሎማሲ ወዳጅነት ቡድን በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር ሀማድ ሞሀመድን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብሎ በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ተወያይቷል።

የውይይቱ ዓላማ የወዳጅነት ቡድኑ አባላት ከአምባሳደሩ ጋር የማስተዋወቅ መርሃ ግብር ማካሄድ፣ በኳታር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች አያያዝ ላይ በጋራ መስራት፣ በተለያዩ ዘርፎችና ተግባራት የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም ማመቻቸት ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም ውይይቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር፣ ትብብርን ማሳደግ እና ፓርላማዎች የሚያበረክቱትን እና በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያግዝ መሆኑም ነው የተመላከተው።

በውይይቱ÷ የኢትዮ-ኳታር ወዳጅነት ቡድን ሰብሳቢ አቶ መሀመድ አል-አሩሲ የሀገራቱ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፤ በሁሉም ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር ሀማድ መሀመድ በበኩላቸው÷ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በሚዲያ፣ በሰራተኛ አያያዝ፣ በኢንቨስትመንት እና በሌሎችም ዘርፎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከውይይቱ በኋላም በኢትዮጵያ የሳይንስ ሙዚየም ጉብኝት መካሄዱን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡