አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ሃገራት ድንበሮቻቸውን ለጎብኝዎች ክፍት እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ።
የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ የአውሮፓ ሃገራት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የዘጉትን ድንበር ለመጭው የአውሮፓውያን የበጋ ወቅት ለጎብኝዎች ክፍት በማድረግ አመታዊውን የጎብኝዎች ወቅት መጠበቅና መጠቀም ይገባል ብሏል።
የአፍ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀምና የተደነገጉ ግዴታዎችን በማስተግበር ድንበሮቻቸውን ቀስ በቀስ እንዲከፍቱም ነው ምክረ ሃሳብ ያቀረበው።
አየር መንገዶችና ትራንስፖርት ሰጭ ድርጅቶች ጎብኝዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረጋቸውን መከታተልና መለየት እንዲሁም ተገቢውን ፍተሻና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የህብረቱ ምክረ ሃሳብ በቱሪዝም ዘርፍ በተሰማሩ አካላት ተቀባይነት ቢያገኝም ከህብረቱ አባል ሃገራት በኩል እስካሁን የተባላ ነገር የለም።
ይሁን እንጅ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገዱ እንደ ስፔን ያሉ ሃገራት ድንበሮቻቸውን በቶሎ እንደማይከፍቱ እየገለጹ ነው።
በወረርሽኙ ሳቢያ በርካታ የአውሮፓ ሃገራትም የሚያከብሯቸውን በዓላት ሰርዘዋል።
ሃገራት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ድንበሮቻቸውን የዘጉ ሲሆን፥ በአውሮፓም ቢያንስ እስከ ፊታችን ሰኔ ወር አጋማሽ ድረስ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ይገመታል።
ቱሪዝም የበርካታ የአውሮፓ ሃገራት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሲሆን፥ ከጎብኝዎች የሚገኘው ገቢ የሃገራቱን 10 በመቶ ኢኮኖሚ እንደሚሸፍን ይነገራል።
ምንጭ፦ ሬውተርስ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።