አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል እና የክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች “ሃብት መፍጠር እና ማስተዳደር” በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ የሚገኙ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኙ።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ”ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በስልጠናው ላይ ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን በዛሬው እለትም በአዳማ ከተማ የሚገኙ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኝተዋል።
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎቹ ስልጠናው ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው፤ በጉብኝታቸውም የኢትዮጵያን እምቅ ሃብቶች መጠቀምና በአግባቡ የማስተዳደር ሂደቶችን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
ሃላፊዎቹ በሁሉም መስክ ያሉ የኢትዮጵያ እምቅ ሃብቶችን በአግባቡ ተረድቶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሀብቶቹን በጋራ አልምቶ መጠቀምና በተገቢው መንገድ ማስተዳደር እንደሚገባም ነው የገለጹት።
በጉብኝታቸው ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ በርካታ የልማት ክንውኖች መኖራቸውን እንዳዩ ጠቅሰው የሀገሪቷን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ አመራሩን ጨምሮ የህዝቡ ትብብርና የጋራ ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በፋብሪካዎች የተመለከትናቸው ሀብት የመፍጠርና የማስተዳደር ልምድ እንዲሁም እንደ ሀገር ሀብቶችን በአግባቡ ማወቅ፣ መጠቀም እና ማስተዳደር የሚቻልበትን ሁኔታ ነው ብለዋል።
የመንግስትን የልማት ፖሊሲዎች በአግባቡ በመተግበር ሀገርን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
“ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተሰጠ ባለው ስልጠናም ኢትዮጵያ ጸጋዎቿን በመጠቀም ለቀጣዩ ትውልድ ዕዳን ሳይሆን ምንዳን ለማስተላለፍ አመራሩ ሌት ተቀን መስራት እንዳለበት የጋራ አቋም የወሰድንበት ነው ያሉት።
ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በአግባቡ ተገንዝቦ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ለሀገር እድገትና ለህዝቦች ተጠቃሚነት በጋራ የሚያነሳሳ ስልጠና መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ሰፊ የመልማት አቅም ያላት በመሆኑ በየአካባቢው ያሉ እምቅ ሃብቶችን በማልማት ወደ ሀገራዊ ሃብት መቀየር እንደሚገባ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።