አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ የሶማሌ ክልል ተወላጆች በጅግጅጋ ከተማ አዲሱ ታይዋን የገበያ ማዕከል ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ንብረታቸው ለወደመባቸው ተጎጂ ነጋዴዎች የ13 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
ድጋፉ ከክልሉ መንግስትና ህዝብ ጎን በመሆን ነጋዴዎቹን ለመደገፍና ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ያለመ ነው ተብሏል።
ድጋፉን የደቡብ ሱዳን የሶማሌ ክልል ተወላጆች ተወካዮች ለሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር ተወካይና ለክልሉ ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ጠይብ አህመድ ማስረከባቸውን ከክልሉ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በጅግጅጋ ከተማ አዲሱ ታይዋን የገበያ ማዕከል በደረሰው የእሳት አደጋ ንብረታቸው የወደመባቸውን ተጎጂዎች መልሶ ለማቋቋም በክልሉ መንግስት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል።