አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአባይ፣ በቆቃ እና በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡
በኢንስቲትዮቱ የትንበያ ባለሙያ ሳምራዊት አበበ÷ በቀጣይ 10 ቀናት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጠንካራ የደመና ሽፋን እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡
በዚህም በፀሐይ ብርሃን የታጀበ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የአየር ትንበያ መረጃ ያመላክታልም ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም የአባይ፣ የቆቃ እና የአዋሽ ወንዞች በመሙላት ከተለመደው ፍሰታቸው ውጪ በመሆኑ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል በመሆኑ ህዝቡ እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል።
በከተሞችም ጎርፍ እንዳይከሰት የፈሳሽ ማስወገጃ ትቦዎችን ከቆሻሻ ማጽዳት እንደሚገባ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
በማርታ ጌታቸው